መላ

ኮምፒውተሬ ለምንድነው ዝግ የሚለው?

ክፍል 1 አላስፈላጊ ፍርግሞች

ብዙ ተጠቃሚዎች ኮምፒውተራቸው ዝግ ይልባቸዋል። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አንዳንዴ ኮምፒውተሩ አውነትም በሚፈለገው ፍጥነት መስራት አይችል የሆናል። ብዙ ጊዜ ግን ኮምፒውተሮችን በጥንቃቄ በመያዝ በጥሩ ፍጥነት እንዲሰሩ ማድረግ ይችላሉ።

መላ በሚያዘጋጀው ተከታታይ ክፍል እንዴት ኮምፒውተርዎ በሚችለው ፍጥናት እንዲሰራ እንደሚያደርጉ፤ በዛውም እንዴት ኮምፒውተርዎን በጥንቃቄ ሊይዙ እንደሚችሉ እናስረዳለን። ነገሮች በደንብ ግልፅ እንዲሆኑ በአንድ ክፍል ላይ አንድ ነገር አንጫወታለን።

ኮምፒውተርዎ ዝግ የሚልበት አንደኛው ምክንያት ብዙ አላስፈላጊ ፍርግሞች (programs) ከተጫኑ ነው። እነዚህን ማራገፍ (uninstall) ጥሩ እርምጃ ነው። በመጀመሪያ መራገፍ ያለባቸውን ፍርግሞች መዝግበው ይያዙ። ከዛም ፍርግሞቹን ያራግፉ።

1. መራገፍ ያለባቸውን ፍርግሞች እንዴት አውቃለሁ?

ይሂ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አላስፈላጊ ፍርግሞች ኮምፒተርዎ ላይ ይኖራሉ። ነገር ግን በግምት ብቻ ፍርግሞችን ቢያራግፉ አስፈላጊ የሆኑ ፍርግሞችም (ለምሳሌ Microsoft Office) አብረው ሊራገፉ ይችላሉ። ስለዚህ የሚያራግፉት ፍርግም አገልግሎቱ ምን እንድሆነ መረዳት አለብዎት።

ዘዴ 1

የማያስፈልጉ ፍርግሞችን ማግኛ አንደኛው ዘዴ ፍርግም ምናሌ (start->program menu) ላይ የተዘረዘሩትን ፍርግሞች ማጥናት ነው። ጀምር->ፍርግሞች ጠቅ ቢያረጉ (click “Start” and then click “Programs”) ኮምፒውተርዎ ላይ የተጫኑ ፍርግሞች ዝርዝር ያገኛሉ። እነዚህን አንድ በአንድ እያከፈቱ ዓላማቸው ምን እንደሆነ ይረዱ። ከነዚህ ውስጥ ለእርስዎ ጠቃሚ ያልሆኑ ፍርግሞች ሊያገኙ ይችላሉ። ጠቃሚ ያልሆኑትን ፍርግሞች ዝርዝር መዝግበው ይያዙ።

ዘዴ 2

ኮምፒውተርዎ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ፍርግሞችን ያንቀሳቅሳል። በአሁኑ ጊዜ እያተንቀሳቀስ ያለ ነገር “ሂደት” (process) ተብሎ ይጠራል። የሂደቶች ቁጥር እየበዛ በመጣ ቁጥር ኮምፒውተርዎ የበለጠ ዝግ እያለ ይመጣል። ሂደቶች አንዳንዴ በአሞሌ ክንውኑ (task bar) ላይ በቀኝ በኩል ይዘረዘራሉ (ልክ ከሰዓቱ በስተግራ በኩል)። ይሚከተለው ምሰል ይህን ያሳያል።

እርስዎ ኮምፒውተር ላይ የተዘረዘሩትን አዶዎች (icons) በደንብ ያጥኑ። ጠቋሚውን ከእያንዳንዱ አዶ ላይ በማሳረፍ፤አንድ ጠክታ ወይም ሁለት ጠቅታ በማድረግ ፍርግሙ ምን ዓላማ እንዳለው ይረዱ። የማያስፈልግ እንደሆነ ስሙን መዝግበው ይያዙ።

ዘዴ 3 ለላቁ (advanced) ተጠቃሚዎች

ይሄ ዘዴ የተወሳሰበ ቢሆንም በጣም ጠቃሚ ዘዴ ነው። “Task Manager” የሚባለውን መስኮት በመክፈት ኮምፒውተርዎ ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሂደቶች በሙሉ መመልከት ይችላሉ። “Task Manager” መስኮትን ለመክፈት እነዚህን ሶስት ቁልፎች በአንድ ላይ ይጫኑ CTRL + ALT + DELETE። አንዳንድ ተጠቃሚዎች ስድስት አዝራሮች (buttons) የያዘ መስኮት ሊያዩ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ “Task Manager” የሚለውን ጠቅ ያርጉ። ሌሎች ተጠቃሚዎች በቀጥታ “Task Manager” መስኮት ይከፈትላቸዋል።

“Task Manager” መስኮት ላይ እያንዳንዱ ረድፍ ስለ አንድ ሂደት ያስረዳል። CPU እና Mem Usage የሚሉት አምዶች (columns) ሂደቱ ምን ያህል ሴፒዩ እና ማህደረ ትውስታ (memory) እየተጠቀመ እንደሆነ ያሳያሉ። የሚከተውን ምስል ይመልከቱ። ብዙ ሲፒዩ ወይም ማህደረ ትውስታ እየተጠቀሙ ያሉትን ሂደቶች በቀላሉ ለመመልከት በቀስቱ ላይ የተመለከቱትን ቦታዎች ይጫኑ። ሂደቶች እንደአጠቃቀማቸው ሽቅብ ይደረደራሉ (sort ascending)። ትልቅ ቁጥር ያለው ብዙ እየተጠቀመ ነው ማለት ነው። ብዙ ጊዜ የሂደቱ ስምና የፍርግሙ ስም ይለያያል። ለምሳሌ MS Word የፍርግም ስም ሲሆን፤ እየተንቀሳቀሰ እያለ Task Manager ላይ WINWORD.EXE በሚል ስም ነው የሚታየው። ስለዚህ የሂደቱን ስም ይዘው በይነመረብ (internet) ላይ ያ ሂደት ምን እንደሆነ የሚያስረዱ ገፆች (web pages) ይፈልጉ። ብዙ ሲፒዩ ወይም ማህደረ ትውስታ የሚወስዱ ሂደቶች አላስፈላጊ ከሆኑ መራገፍ አለባቸው።

2. ፍርግሞችን እንዴት ነው የማራግፈው?

ለዚህ እራሱን የቻለ ዓምድ ተዘግጅትዋል። ከመላ ድር ጣቢያ ላይ www.mela.ertale.com ማውረድ ይችላሉ።

3. ምክር

1. ኮምፒውተር መጀመሪያውኑ ሲገዛ አንዳንድ አላስፈላጊ ፍርግሞች ተጭናውበት ይመጣል። ኮምፒውተሩን የሚሸጥልዎትን ሰው የሚጫኑት ፍርግሞች ዝርዝር እንዲነግረዎትና የማያስፈልግዎት ፍርግም እንዳይጫን ይነጋገሩ።

2. “አንድ ጊዜ እፈልገው ይሆናል” በማለት ያገኙትን ፍርግም ሁሉ አይጫኑ።

3. በሲዲ የገዙት ወይም ከኢንተርኔት ላይ ያወረዱት (download) ፍርግም ካለ ሲዲውን ወይም ያወረዲትን ፋይል በጥንቃቄ ያስቀምጡ። ፍርግሙ በሚያስፈልግዎት ጊዜ ሊጭኑት ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር፤ ኮምፒውተርዎ ቢበላሽና እንደገና ሁሉ ነገር መጫን ቢኖርበት ፍርግሞቹን ሌላ ቦታ (ለምሳሌ በሲዲ) አስቀምጠው ክሆነ በቀላሉ መልሰው ሊጭኑአቸው ይችላሉ።

4. ኮምፒውተርዎ እስኪበላሽ አይጠብቁ። በየጊዜው እዚህ የተጠቀሱትን ነጥቦች እንደገና ያድርጉ።

5. የኮምፒውተር ችግር ሲያጋጥሞት ድር ጣቢያችንን ይጎብኙ።

6. ችግር ካጋጠምዎት ጥያቄዎትን talk.ertale.com ላይ ያቅርቡ።

ትርጉም*

መስኮት window

መጫን install ማራገፍ uninstall ማንቀሳቀስ run

ምናሌ program menu ሽቅብ መደርደር sort ascending ቁልፍ keyboard key

በይነመረብ internet አዶ icon ድር ጣቢያ web site ጀምር Start button

ጠቅ ማረግ click ጠቋሚ pointer/cursor ፍርግም program

*አዚህ ፅሑፍ ላይ የሚገኙት ቃላት (እንደ “ፍርግም”፣”ማራገፍ”ና የመሳሰሉት) የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ባወጣው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

መላ

ፅሑፉ ጥሩ ነበር? ይሂን ተከታታይስ ስንጨርስ ስለምን እንድንፅፍ ይፈልጋሉ? ሃሳብዎትን ለመግለፅ፤ ቀጣዩን ክፍል ለማውረድና የራስዎትን ጥያቄ ለመጠየቅ ኢሜይል ያድርጉልን፤ ወይም ድር ጣቢያችንን ይጎብኙ።

mela@ertale.com www.mela.ertale.com

ይህ ፅሑፍ ነፃ ነው። ይዘቱን በምንም ዓይነት መንገድ ሳይቀይሩ ማባዛት ይቻላል።

ፅሑፉን ለማውረድ

መላ

ፍርግሞች እንዴት ነው የሚራገፉት?

ታደሰ – አንድ ፍርግም (program) አላስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እንዴት ይኖን የማራግፈው (uninstall)?

አዜብ – ዝምብለህ የፍርግሙን አዶ (icon) ብትሰረዘውስ (delete)?

1. ማራገፍ

1 የሚያራግፉትን ፍርግም ይወቁ

የሚያራግፉት ፍርግም ስሙ ምን እንደሆን ይወቁ። ለአርስዎም አስፈላጊ እንዳልሆነ ያረጋግጡ። ፍርግሙን ካራገፉ በሁዋላ መልሰው መጫን ቢፈልጉ ተጫኝ ፍርግሙ (setup program) ያስፈልግዎታል። ስለዚህ የበለጠ ለማወቅ “ፍርግሞችን እንዴት ነው የሚጫኑት?” የሚለውን ዓምድ ያንብቡ።

2 ፍርግሙን ያራግፉ

ዘዴ 1

ፍርግሙን ከመክፈቻ ምናሌ (start menu) ላይ ይፈልጉት። አንዳንድ ፍርግሞች መክፈቻ ምናሌው ላይ “አራግፍ” (uninstall) የሚል አማራጭ አላቸው። ይሄን ካገኙ ጠቅ ያርጉትና የሚከፈትዉን መስኮት ይከተሉ።

ዘዴ 2

Add or Remove Program መስኮትን ይክፈቱ፤

Start -> Control Panel -> Add or Remove Program

እዚህ መስኮት ላይ ለማራገፍ የሚፈልጉትን ፍርግም ይፈልጉና ይምረጡት (select)። ፍርግሙን ሲመርጡት አራግፍ (remove)፤ አስወግድ (remove) ወይም ተመሳሳይ ምርጫ የሚሰጥ አዝራር (button) ይመጣልዎታል። ይሄን አዝራር ጠቅ ያርጉና የሚከፈተዉን መስኮት ይከተሉ።

3 መራገፉን ለማረጋገጥ

ፍርግሙ መራገፉን ለማረጋገጥ መክፈቻ ምናሌ (start menu) ላይ ፍርግሙን ይፈልጉት። ብዙ ፍርግሞች በትክክል ከተራገፉ ከመክፈቻ ምናሌው ላይ ይጠፋሉ።

2. ምክር

1. Add or Remove Program መስኮት ላይ ከወደላይ ቀኝ በኩል “ደርደር” (sort) የሚል አማራጭ አለ። ፍርግሞችን በአጠቃቀምዎ ብዛት ሊደረድሩዋቸው ይችላሉ። ብዙ የማይጠቀሙት ፍርግም የትኛው እንደሆን ከዚህ ሊረዱ ይችላሉ። በመጠንም (size) ሊደረድርዋቸው ይችላሉ። ብዙ አቅመ ዲስክ (disk space) እየወሰዱ ያሉትን ፍርግሞች በቀላሉ ሊያገኙ ይችላሉ።

2. የፍርግምን አዶ መሰረዝ ፍርግሙን አያራግፈውም።

3. ችግር ካጋጠምዎት ጥያቄዎትን talk.ertale.com ላይ ያቅርቡ።


ትርጉም*

መምረጥ select መሰረዝ delete መክፈቻ ምናሌ start menu መደርደር sort

መጠን size ማስወግድ remove ማራግፍ remove ማራገፍ uninstall

ምናሌ start menu ተጫኝ ፍርግም setup program አቅመ ዲስክ disk space

አዝራር button አዶ icon ፍርግም program

*አዚህ ፅሑፍ ላይ የሚገኙት ቃላት (እንደ “ፍርግም”፣”ማራገፍ”ና የመሳሰሉት) የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ባወጣው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

መላ

ፅሑፉ ጥሩ ነበር? በሚቀጥለው ዓምድ ስለምን እንድንፅፍ ይፈልጋሉ? ሃሳብዎትን ለመግለፅ፤ ተከታዩን ዓምድ ለማውረድና የራስዎትን ጥያቄ ለመጠየቅ ኢሜይል ያድርጉልን፤ ወይም ድር ጣቢያችንን ይጎብኙ።

mela@ertale.com www.mela.ertale.com

ይህ ፅሑፍ ነፃ ነው። ይዘቱን በምንም ዓይነት መንገድ እስካልቀየሩ ድረስ ማባዛት ይቻላል።

ፅሑፉን ለማውረድ

መላ

ፍርግሞች እንዴት ነው የሚጫኑት?

ተጠቃሚዎች ፍርግሞችን መጫን የተወሳስበ ነገር አድርገው ያስቡታል። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ መሠረታዊ የኮምፒውተር እውቀት ያለው ተጠቃሚ ፍርግሞችን መጫን ይችላል። እዚህ ዓምድ ላይ ለመጫን ምን ምን ማድረግ እንዳለብዎት አንድ በአንድ እንጫወታለን።

ፍርግሞችን መጫን

1 ተጫኝ ፍርግሙን ያዘጋጁ

አንድ ፍርግም ሲጫን አስፈለጊ የሆኑ ፋይሎች በሙሉ ወደ ኮምፒውተርዎ ይቀዳሉ። እንዚህ ፋይሎች ኮምፒውተርዎ ላይ የተለያየ ቦታ ይገባሉ። ፍርግሙን በቀላሉ መክፈት እንዲችሉም አቁዋራጮች (shortcut) ይፈጠራሉ (ለምሳሌ ዴስክቶፕ ላይ)። የሄን ሁሉ የሚያረግ ፍርግም “ተጫኝ ፍርግም” (setup program) ያስፈልጋል።

አንድ ኮምፒውተር ላይ Microsoft Word ተጭኖ እንደሆነ፤ ከሱ ኮምፒውተር ላይ Microsoft Wordን ቀድቶ (copy) ወደሌላ ኮምፒውተር ላይ መለጠፍ (paste) አይቻልም። እርግጥ አንዳንዴ ይሄ የሚሠራበት ጊዜ አለ። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ተጫኝ ፍርግም ያስፈልጋል።

ብዙ ፍርግሞች ተጫኝ ፍርግማቸው በሲዲ ይገኛል። ለምሳሌ የMicrosoft Office (Microsot Word፣ Microsoft Excel እና የመሳሰሉትን አጠቃሎ ይይዛል) ተጫኝ ፍግም በሲዲ ይመጣል። ከበይነመረብ (internet) ላይም የሚገኙ ተጫኝ ፍርግሞች አሉ። ስለዚህ መጫን የሚፈልጉትን ፍርግም ይወቁና የሱን ተጫኝ ፍርግም ያግኙ።

2 ፍርግሙን ይጫኑ

ተጫኝ ፍርግሙ ላይ መጫኛ ፈይሉን ይፈልጉና ይክፈቱት። አብዛኛዉን ጊዜ መጫኛ ፋይሉ setup.exe ወይም install.exe የሚል ስም ይኖረዋል፤ ወይም በፍግሙ ስም ተሰይሞ ይሆናል።

ተጫኝ ፍርግሞች ሲከፈቱ ብዙ ጊዜ ወደሁዋላ (back)፣ ቀጥል (next) እና ጨርስ (finish) የሚሉ አማራጮች ይኖራቸዋል። ተጫኝ ፍርግሞች በመጀመሪያ የተለያዩ ጥያቀዎች ይጠይቁዎታል።

አማራጮች በሙሉ ተራ በተራ በተለያዩ መስኮቶች ይቀርባሉ። እርስዎ የመጣልዎት መስኮት ላይ ያሉትን አማራጮች አይተው፤ ከፈለጉም ቀይረው፤ “ቀጥል” የሚለውን አዝራር (button) ጠቅ ያረጋሉ። ሃሳብዎን ከቀያሩ “ወደሁዋላ” (back) የሙለዉን አዝራር ጠቅ አርገው ሌላ ምርጫ መስጠት ይችላሉ። የሚመጡልዎት አያራጮች የሚጫነውን ፍርግም ባህርይ (features)፤ የሚጫንበትን ቦታና የመሳሰሉትን የሚጠይቁ ናቸው። “ነባሪ” (default) አማራጮች ተጫኝ ፍርግሙ ለአርስዎ የመረጣቸው አማራጮች ናቸው። እንዚህ አማራጮች ለብዙ ተጠቃሚዎች ያስፈልጋሉ ተብለው የታሰቡ ስለሆን እነሱን የመቀየር ፍላጎት ከሌልዎት የተመረጡትን ነባሪ ምርጫዎች እንዳሉ ሊቀበሉዋቸው ይችላሉ።

ተጫኝ ፍርግሙ ምርጫዎችዎን በሙሉ ከሰበሰበ ብሁዋላ ፍርግሙን ሊጭን እንደሆነ ያስታውቅዎታል። ይሄን ጊዜ “ጨርስ” ወይም “ጫን” የሚል አዝራር ይቀርብሎታል። እሱን ሲጫኑ ፍርግሙ መጫን ይገምራል።

ፍርግሞችን መጫን ከጥቂት ሰኮንዶች እስከ ሰዓታት ሊፈጅ ይችላል። የሚያስፈልገው ጊዜ በአብዛኛው የሚወሰነው በፍርግሙ ትልቅነትና በኮምፒውተርዎ ፍጥነት ነው።

ተጫኝ ፍርግሙ ጭኖ ሲጨርስ በትክክል መጫኑን የሚሳያ መስኮት ያሳይዎታል። ኮምፒውተርዎን እንደገና መጀመር (restart) ያስፈልግዎት እንደሆነም ይነግርዎታል።


3 ፍርግሙን ይሞክሩ

ፍርግሙ ተጭኖ ሲጨርስ ሁሉ ነገር በደንብ መሥራቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለጫኑት ፍርግም ከደስክቶፑ ያል ወይም ከመክፈቻ ምናሌ (start menu) ላይ ፈልገው ይክፈቱና የተለያዩ ነገሮችን ሞካክረው በደንብ መስራቱን ይሞክሩ። ችግር ካለ ተጫኝ ፍርግሙን እንደገና ከፍተው ለመጫን ይሞክሩ።

2. ምክር

1. ፍርግሞች ሁል ጊዜ የሚጫኑበት ኮምፒውተር የተወሰኑ መስፈርቶች (requirement) እንዲያሙዋላ ይፈልጋሉ። መስፈርቶቹ አቅመ ዲስክ (disk space)፣ ማህደረ ትውስታ (memory)፣ ሲፒዩ፣ ስርዓተ ክወና (operating system) እና የመሳሰሉትን ያካትታሉ። ብዙ ጊዜ ለዚህ መጨነቅ አያስፈልግዎትም። ፍርግሙን ከጫኑ በሁዋላ ግን ፍርግሙን ሲከፍቱት ኮምፒውተርዎ ለምሳሌ ዝግ ቢል፤ ኮምፒውተርዎ መሥፈርቱን ሳያሙዋላ ቀርቶ ሊሆን እንደሚችል ይወቁ።

2. ተጫኝ ፍርግሙን ጠንቅቀው ያስቀምጡ። ፍርግሙ ወደፊት ቢበላሽ ወይም ኮምፒውተርዎ እንደገና መጫን ቢኖርበት ተጫኝ ፍርግሙን በመጠቀም ፍርግሙን እንደገና ሊጭኑት ይችላሉ።

3. የኮምፒውተር ችግር ሲፈጠር ኮምፒውተሩ ላይ በቅርቡ ምን ለውጥ እንደተደረገ ማወቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ አንድ ፍርግም ከጫኑ በሁዋላ ኮምፒውተርዎ ላይ ለውጥ ቢያዩ፤ ቀስ ቢል ወይም መልክተ ስህተት ቢያዩ በቅርቡ ከተያያዘው ፍርግም ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይጠርጥሩ።

4. ችግር ካጋጠምዎት ጥያቄዎትን talk.ertale.com ላይ ያቅርቡ።

ትርጉም*

መለጠፍ paste መክፈቻ ምናሌ start menu መጀመር restart መስፈርቶች requirement

መቅዳት copy ማህደረ ትውስታ memory ተጫኝ ፍርግም setup program

ቀጥል next ቀጥል next በይነመረብ internet አዝራር button

አቅመ ዲስክ disk space አቁዋራጭ shortcut

ነባሪ default ወደሁዋላ back ዲስክ disk space ጨርስ finish

*አዚህ ፅሑፍ ላይ የሚገኙት ቃላት (እንደ “ፍርግም”፣”ማራገፍ”ና የመሳሰሉት) የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ባወጣው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

መላ

ፅሑፉ ጥሩ ነበር? በሚቀጥለው ዓምድ ስለምን እንድንፅፍ ይፈልጋሉ? ሃሳብዎትን ለመግለፅ፤ ተከታዩን ዓምድ ለማውረድና የራስዎትን ጥያቄ ለመጠየቅ ኢሜይል ያድርጉልን፤ ወይም ድር ጣቢያችንን ይጎብኙ።

mela@ertale.com www.mela.ertale.com

ይህ ፅሑፍ ነፃ ነው። ይዘቱን በምንም ዓይነት መንገድ እስካልቀየሩ ድረስ ማባዛት ይቻላል።

ፅሑፉን ለማውረድ